መዝሙር

መዝሙር 118
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ናትና።
² ቸር እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ ለዘላለም እንደ ሆነች የእስራኤል ቤት አሁን ይንገሩ።
³ ቸር እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ ለዘላለም እንደ ሆነች የአሮን ቤት አሁን ይንገሩ።
⁴ ቸር እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ ለዘላለም እንደ ሆነች እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ አሁን ይንገሩ።
⁵ በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ ሰማኝ አሰፋልኝም።
⁶ እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፥ አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል?
⁷ እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፥ እኔም በጠላቶቼ ላይ አያለሁ።
⁸ በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።
⁹ በገዦች ተስፋ ከማድረግ ይልቅ በእግዚአብሔር ተስፋ ማድረግ ይሻላል።
¹⁰ አሕዛብ ሁሉ ከበቡኝ፥ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው፤
¹¹ መክበቡንስ ከበቡኝ፥ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው፤
¹² ንብ ማርን እንዲከብብ ከበቡኝ፥ እሳትም በእሾህ ውስጥ እንዲነድድ ነደዱ፥ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው።
¹³ ገፋኸኝ፥ ለመውደቅም ተንገዳገድሁ፤ እግዚአብሔር ግን አገዘኝ።
¹⁴ ኃይሌም ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ እርሱም መድኃኒት ሆነልኝ።
¹⁵ የእልልታና የመድኃኒት ድምፅ በጻድቃን ድንኳን ነው፤ የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች።
¹⁶ የእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ አደረገችኝ፤ የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች።
¹⁷ አልሞትም በሕይወት እኖራለሁ እንጂ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ እናገራለሁ።
¹⁸ መገሠጽስ እግዚአብሔር ገሠጸኝ፤ ለሞት ግን አልሰጠኝም።
¹⁹ የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ፤ ወደ እነርሱ ገብቼ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።
²⁰ ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት፤ ወደ እርስዋ ጻድቃን ይገባሉ።
²¹ ሰምተኸኛልና፥ መድኃኒትም ሆነኸኛልና አመሰግንሃለሁ።
²² ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፥ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤
²³ ይህች ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነች፥ ለዓይናችንም ድንቅ ናት።
²⁴ እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን።
²⁵ አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን፤ አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና።
²⁶ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ ከእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ።
²⁷ እግዚአብሔር አምላክ ነው፥ ለእኛም በራልን፤ እስከ መሠዊያው ቀንዶች ድረስ የበዓሉን መሥዋዕት በገመድ እሰሩት።
²⁸ አንተ አምላኬ ነህ አመሰግንህማለሁ። አንተ አምላኬ ነህ፥ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ሰምተኸኛልና፥ መድኃኒትም ሆነኸኛልና አመሰግንሃለሁ።
²⁹ እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ናትና። 11

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *